Home / Social Affairs / በአማራ ክልል በበርካታ አከባቢዎች የጸጥታ ችግሮች መስተዋላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ፤ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፣ በረራዎች ተስተጓጉለዋል

በአማራ ክልል በበርካታ አከባቢዎች የጸጥታ ችግሮች መስተዋላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ፤ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፣ በረራዎች ተስተጓጉለዋል

በአማራ ክልል በርካታ አከባቢዎቸ የጸጥታ መደፍረስ እየተስተዋለ እንደሚገኝ እና አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ። ከሁለት አመት አጋማሽ ጀምሮ ግጭትና ጦርነት በማስተናገድ የሚገኘው የሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ ነዋሪዎች በሳምንቱ መጀመሪያ ጀምሮ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ለከተማው ቅርብ በሆኑ የገጠር አከባቢዎች እንደሚሰማ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ግጭቱ በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ የፋኖ አባላት እና በሀገሪቱ የመከላከያ ሀይል መካከል መሆኑን ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።

የቆቦ ከተማ ነዋሪ የሆነችው እና ስሟ ለደህንነቷ ሲባል እንዳይገለጽ የጠየቀችን ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቀችው ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ ጀምሮ በከተማው በቅርብ እርቀት እስከ ንጋት ድረስ የዘለቀ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር ተናግራለች።

ከፍተኛ የሆነ የመከላከያ እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጸችልን የከተማዋ ነዋሪ የመከላከያ ሀይሎች በመኪና ላይ የተጠመዱ ትላልቅ መሳሪያዎችን ጭኖ ሲያልፍ መመልከቷን አስታውቃለች።

በተመሳሳይ መንገሻ የተባለ የከተማ ነዋሪ የሆነ ከአዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በድንገተኛ ሞት የተለየውን ጓደኛውን አስከሬን ይዞ ወደ ሰሜን ወሎ ቆቦ ከተማ መጓዙን ገልጾ ከአዲስ አበባ በደብረብርሃን ደሴ መንገድ ተጠቅመን እንዳንሄድ መንገዱ በጸጥታ ችግር በመዘጋቱ በአፋር በኩል ዙሪያ ጥምጥም ብዙ ኪሎሜትር እንድንጓዝ ተገደናል ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። በከተማዋ በዛሬው ዕለትም የባጃጆች እንቅስቃሴ በመከላከያ ወታደሮች መከልከል መጀመሩን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቋል።

ወደ ክልሉ ከተሞች የሚደረጉ በረራዎች መስተጓጎላቸውን የተመለከቱ መረጃዎችም እየወጡ ይገኛሉ። በላሊበለ ከተማ ዙሪያ በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን እና ወደ ከተማዋ የተደረገ የአውሮፕላን በረራ በዚህም ሳቢያ መስተጓጎሉን ቢቢሲ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። በዛሬው እለት ወደ ጎንደር ሊጓዙ የነበሩ አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት በረራው ተሰርዟል መባላቸውን እና ተለዋጭ ቀጠሮ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።

ከክልሉ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን ስራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ በፌስቡክ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ይህንን አረጋግጠዋል። በተጨማሪም በመልዕክታቸው የአቢይ አሕመድ አስተዳደር በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራና የንፁኃን ግድያ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳስበዋል። የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ እንዲሁም ሚዲያዎች መንግስት የቴሌኮም አገልግሎቶችን በመዝጋት ጭምር በአማራ ክልል በከባድ መሣሪያ ታግዞ በንፁኃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋ እንድታወግዙና አገዛዙ ላይ ጫና እንድታሳድሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ባሰራጨው ዘገባ በክልሉ እየተስተዋለ ያለው ግጭት በበርካታ አከባቢዎች እየተስፋፋ እንደሚገኝ እና በሰዎች ላይም ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።  የፋኖ አባላት በርካታ ከተሞችን ተቆጣጠሩ የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ በመሰራጨት ላይ የሚገኝ ሲሆን ሮይተርስ የዜና ወኪል የዲፕሎማሲ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ በፋኖ ቁጥጥር ስር እንደምትገኝ በዘገባው አስታውቋል። የስፔን ኤምባሲ በላሊበላ ከተማ በተለያዩ ምክንያት የገቡ ዜጎቹ ከሆቴል ክፍላቸው እንዳይወጡ የሚያሳስብ መግለጫ ማውጣቱን የዜና ወኪሉ አካቷል። በደብረታቦር በተካሄደ የመከላከያ እና የፋኖ አባላት ግጭት ሶስት ሰዎች በከባዱ ቆስለው አስር ሰዎች ደግሞ ቀላል ጉዳት አስተናግደው ሆስፒታል መታከማቸውን ከሆስፒታሉ ደክተሮች ያገኘውን መረጃ አስታኮ የዜና አውታሩ በዘገባው አስታውቋል። ከሆስፒታሉ ዶክተሮች በተጨማሪ በከተማዋ ከሚገኙ ፖሊሶችም መረጃውን ማረጋገጡን አመላክቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *