Home / Social Affairs / በአማራ ክልል ነዋሪዎች በዘፈቀደ ተገድለዋል

በአማራ ክልል ነዋሪዎች በዘፈቀደ ተገድለዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/2016 ዓ.ም፡- በአመራ ክልል ከህግ አግባብ ውጭ የሚካሄዱ ግድያዎች እንዲቆሙ እና አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ አምነስቲ ባወጣው ሪፖርት ጠየቀ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በባህርዳር ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ ነዋሪዎችን ገድለዋል ሲል የገለጸው አምነስቲ በአንዳንድ ቦታዎች የሟቾች ቤተሰቦች የሟቾቹን አስከሬን በማንሳት እንዳይቀብሩ ተከልክለዋል ሲል ኮንኗል።

በከተማዋ መንገዶች የሟቾች አስከሬን ለሰአታት እንዳይነሳ ተደርጓል ሲሉ የከተማዋ ነዋሪ እና የአይን እማኞች እንደነገሩት በሪፖርቱ አካቷል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት በባህርዳር አቡነ ሀራ እና ልደታ አጎራባች በሆኑ ቀበሌዎች ስድስት ሰዎችን በዘፈቀደ ከህግ አግባብ ውጭ መግደላቸውን ያሰባሰባቸውብ መረጃዎች በመጥቀስ ያስታወቀው አምነስቲ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ በከተማዋ ሰባታሚት አጎራባች የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ሌሎች ስድስት ሰዎችን መግደላቸውንም ጠቁሟል፤ ግድያዎቹ የተፈጸሙት ባሳለፍነው አመት ነሃሴ ወር እና በያዝነው አመት ጥቅምት ላይ መሆኑን ገልጿል።

በክልሉ የተፈጸሙ ግድያዎች እና ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ቀስበቀስ መውጣት መጀመራቸውን ያስታወቀው አምነስቲ በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ፣ በከፊል የኮሙዩኒኬሽን መንገዶች በመዘጋታቸው እና በክልሉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጁን በምክንያትነት አስቀምጧል።

በክልሉ እና በዋና ከተማዋ የሚካሄደውን በትጥቅ የተደገፈ ግጭት ተከትሎ በመፈጸም ላይ ያሉ ግድያዎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአፋጣኝ በገለልተኛ ወገን እንዲመረመር የአምነስቲ የምስራቅ እና ደቡባዊ ቀጠና ዋና ዳይሬክተር ቲገረ ቻጉታህ መጠየቃቸውን ሪፖርቲ አካቷል።

በባህርዳር መበከላከያ ሰራዊት አባላት ግድያው የተፈጸመው በቅርብ ርቀት በተተኮሰ ጥይት መሆኑን ከሟች ቤተሰቦች እና የአይን ምስክሮች ያገኘሁት መረጃ ያሳያል ብሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *