የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ አምባሳደር ኤርቨን ማሲንጋ በኩል፣ ግንቦት 15 2017 ዓ.ም ዕለት ያስተላለፉትን ጥሪ በአንክሮ ተመልክቶታል፡፡
በቅድሚያ፣ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በመላው ዓለም ያሉ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደምናደንቅ እና ለዚህም ሰኬትን እንደምንመኝ መግለጽ እንወዳለን፡፡
በአምባሳደር ማሲንንጋ መልዕክት ላይ እንደተመለከትነው፣ “ፋኖ ተጨባጭ እና ሰላማዊ የሆነ አማራጭ ይዞ ይምጣ” የሚል ጥሪ ቀርቧል። ይህ ጥሪ ግን፣ የሚታገልለትን ዓላማ በማኒፌስቶ ደረጃ ግልጽ ያደረገውን እና ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ ወኪሎች ጋር በአካል ተገናኝተቶ ዝርዝር አማራጮችን በፅሁፍ ያቀረበውን አፋህድ የማይመለከት ነው ብለን ወስደውናል።
ሆኖም፣ የአሜሪካው አምባሳደር በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በቀጥታ ሊያገኙን የሚፈልጉ ከሆነ፣ በራችን ክፍት መሆኑን መግለፅ እንወዳለን።
አምባሳደር ማሲንጋ ባስተላለፉት ቀዳሚ መልዕክታቸው ፣ “የፌዴራል መንግሥቱ በራሱ ዜጎች ላይ የሚያደርገውን የድሮን ጥቃት በአስቸኳይ ያቁም” በማለት መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚገልጽ፤ የሕዝባችንን ህመም የሚጋራ መልዕክት አስተላልፈው የነበረ ቢሆንም፣ ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ በሰዓታት ልዩነት ይህ የመልዕክታቸው ጭብጥ እንዲወጣ መደረጉን ተመልክተናል፡፡
ይህ መሆኑ አሜሪካ ለዘመናት ያዳበረችውን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነት እና በመላው ዓለም ያሉ ግጨቶችን እና ጦርነቶችን በሰላም ለመፍታት እያደረገች የምትገኘውን ሰፊ ጥረት የሚያግዝ ሆኖ አላገኘነውም። እንዲያውም፣ በተቃራኒው፣ አገዛዙ በግትር የጦረኝነት እና የጨፍጫፊነት ፖሊሲው እንዲፀና፣ እራሳቸውን ከመንግሥታዊ የጅምላ ጭፍጨፋ እየተከላከሉ የሚገኙትን ተፋላሚዎቹን ደግሞ ተጠራጣሪ እንዳያደርጋቸው ስጋት አለን።


ስለሆነም፡-
1— የብልጽግና አገዛዝ በራሱ ዜጎች ላይ የድሮን ጥቃት እንዲያቆም የተጠየቀው ፍትሃዊ በመሆኑ፣ አሜሪካ በዚህ አቋሟ እንድትፀና እንጠይቃለን፣
2 — የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ ሌሎች የጦር ወንጀሎችንም የሚመረምር ገለልተኛ የሆነ ዓለምአቀፋዊ አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም እና በውጤቱ መሠረት ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፣
3 — በአጠቃለይ ዓለም-አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ ትግል፣ በተለይም ይዘቱ ልዩ የሆነውን የአማራ ሕዝብን የፀረ-ጄኖሳይድ የህልውና ትግል በአግባቡ እንዲረዳው እና ጥርት ያለ አቋም እንዲይዝ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ክሽፈት በሀገራዊ ደረጃ ከመወሰን አልፎ ወደ ጂኦ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እያደገ ያለው በአጠቃላይ ብሄር ተኮር፣ በተለይ ደግሞ አማራ ጠል በሆነው የብልፅግና ፓርቲ የአጥፍቶ መጥፋት ፖለቲካ እንደሆነ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሰወረ ባለመሆኑ፣ በዚህ ልክ መፍትሄ እንዲመጣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት መናበብ አና ተቀናጅቶ መሥራት ግድ ይላል።
ስለዚህም፣ አማራ ላይ ያነጣጠረውን ብሄር ተኮር የገዢው ፓርቲ የጥላቻ ፖለቲካ ከስር መሠረቱ የሚነቅል የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ እና የአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላ የኢትዮጵያ ህዝብም ለ50 ዓመታት የናፈቁትን ሰላም እና ሥር-ነቀል ለውጥ እንዲጎናፀፉ ለማገዝ፣ በአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ፈር ቀዳጅነት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከሚያደርጋቸው አዎንታዊ ጥረቶች ጋር ለመተባበር እንደ ወትሮው በቅንነት ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።
ድል ለአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት!!
ድል ለአማራ ህዝብ!!
ድል ለኢትዮጰያ ህዝብ!!
የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት
ግንቦት 16፣ 2017 ዓ. ም