Home / Social Affairs / የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ መቀመጫቸው አዲስ አበባ የሆነ 14 ኤምባሲዎች በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ እንዳሳሰባቸው ገለጹ

የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ መቀመጫቸው አዲስ አበባ የሆነ 14 ኤምባሲዎች በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ እንዳሳሰባቸው ገለጹ

የአለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በየአመቱ ሚያዚያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም መከበርን አስመልክቶ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም መቀመጫቸው አዲስ አበባ የሆነ 14 ኤምባሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ እጅግ እንዳሳሰባቸው አስታወቁ።

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ቡድነ በበኩሉ የዘንድሮን የ2025 እ.አ.አ የሀገራትን የፕሬስ ነጻነት አስመልክቶ ባወጣው ደረጃ እና ሪፖርት “የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን” አስታውቋል፤ ከ100 ነጥብ ውስጥ 36 ነጥብ 92 በማስመዝገብ 180 ሀገራት መካከል 145ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት እንደሚገኝ አስተውለናል፣ አሳሳቢም ነው ሲሉ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፍራንስ፣ ኖርዌይ፣ ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ስዊዲን፣ አየርላንድ፣ ስፔን፣  ሉክሰንበርግ፣ ኔዘርላንድ፣ አውስትራልያ፣ ስሎቫንያ፣ ፊንላንድ እና  ኒውዝላንድ ዛሬ ሚያዚያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በጋራ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ዕለቱን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ “የፕሬስ ነፃነት እጦት መረጃ የማግኘት መብትን እና የመተቸት ነፃነትን ያጓድላል” ሲል አሳስቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተላቸው የልማት ግቦችን እና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለማሳካት የፕሬስ ነፃነት ትልቅ ሚና ይጫወታል ሲል ምክረ ሀሳቡን አስቀምጧል።

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ቡድነ በበኩሉ የዘንድሮን የ2025 የሀገራትን የፕሬስ ነጻነት አስመልክቶ ባወጣው ደረጃ እና ሪፖርት “የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን” አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው በአለም የፕሬስ ነጻነት መመዘኛ ደረጃ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት በአራት ደረጃ አሽቆልቁላ ከ180 ሀገራት መካከል 145ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ቡድኑ በሪፖርቱ አመላክቷል።

አምና ኢትዮጵያ ከ180 ሀገራት ውስጥ 141ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ አራት ደረጃዎችን በማሽቆልቆል 145ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኖርዌይ በአለም አንደኛ የፕሬስ ነጻነት ያለባት ሀገር ተብላ 92 ነጥብ 31 ስታስመዘግብ ኤርትራ የመጨረሻ ደረጃን በመያዝ 11 ነጥብ 32 በማስመዝገብ የመጨረሻውን 180ኛ ደረጃ ይዛለች ተብሏል።

በተያዘው በ2025 ምንመ አይነት ግድያ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ላይ አልተፈጸመም ያለው ተቋሙ አምስት ጋዜጠኞች ግን በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

በትግራይና በአማራ ክልሎች በተካሄደው ጦርነት የመንግስትን አቋም ያልደገፉ በርካታ ጋዜጠኞች “ሽብርተኝነትን በማበረታታት” በሚሉ ከባድ ክሶች ተይዘው በምድረ በዳ በሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ለወራት መታሰራቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በርካታ ጋዜጠኞች ግጭቶችን በመዘገባቸው ምክንያት አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጾ ሥራቸውን መቀጠል ባለመቻላቸው አንዳንዶቹ አገሪቱን ለቀው እስከመውጣት መድረሳቸውን አመልክቷል።

ሪፖርቱ በግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፕሬስ ነፃነት ያስመዘገበችው እድገት ተቀልብሷል ብሏል።

በጎርጎሮሳውያኑ 2022 የትግራይ ጦርነትን በይፋ ያጠናቀቀውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተከትሎ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት በጋዜጠኞች ዘንድ የበቀል እርምጃ ይወሰድብናል የሚለውን ስጋት እና ፍራቻ እንዳባባሰው አመልክቷል።

በጦርነቱ ላይ ያለውን ሁኔታ ለመቆጣጠር ሲባል በታጣቂዎችም ሆነ በመንግስት አካላት የሚካሄደው ፕሮፓጋንዳ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሀሰተኛ መረጃ መስፋፋትን ፈጥሯል ብሏል።

በመንግሥት በኩልም የግጭቶቹን ሁኔታ ለመቆጣጠር በማሰብ “የፋክት ቸኪንግ” መድረክ መፍጠሩን ገልጾ ሆኖም መድረኩ በመሠረታዊነት የመንግሥትን መልዕክት ለማስተላለፍ የሚያገለግል የሐሰት መረጃዎችን በመጠቀም ተቃዋሚዎችን ለማጣጣል እንደሚያገለግል አስታውቋል።

በጎርጎሮሳውያኑ በ2021 የፀደቀው አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ለጋዜጠኞች ይበልጥ ጥበቃን የሰጠ ይሁን እንጂ በተግባር የጋዜጠኞችን እስር አላስቀረም ሲል ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ሪፖርቱ አክሎም የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ እና በቅርቡ የጥላቻ ንግግር አስመልክቶ የወጣው  ሕግ በጣም አሻሚ የሆኑ ድንጋጌዎችን ያካተቱ መሆናቸውን ጠቅሶ ህጎቹ ከባባድ የእስር ቅጣቶችን የሚያስከትሉ እና በግልጽ የሚናገሩ ጋዜጠኞችን ለማፈን ሊያገለግሉ ይችላሉ ብሏል።

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC) በበኩሉ ትላንት ሚያዚያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ጫናዎች እየበረቱ መምጣታቸውን በመግለጽ እጅግ አሳስቦኛል ብሏል።

“በኢትዮጵያ የሚድያ ምህዳር ውስጥ ለአመታት የቆየው አዲስ ስታንዳርድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ላይ ሚያዚያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በህግ አስከባሪ አካላት ብርበራ እና የሚዲያ ስራ የሚሰራባቸው መገልገያዎች መወሰድን” የተቋሙ ሰራተኞች ለሰዓታት መታሰራቸውን በአብነት አስቀምጧል።

ድርጊቱ “የመገናኛ ብዙሃን ህጉን የሚፃረሩ፤ ጋዜጠኞች በህብረተሰቡ ውስጥ የሚጫዎቱትን ሚና የሚያቀጭጩ እና ተጠያቂነት እንዳይኖር የሚያደረጉ ናቸው ብሎ ያምናል” ብሏል።

 “መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን እና የተሻሻለው የመገናኛ ብዙሃን ህግ የሚዲያ ምህዳሩን ክፉኛ ይጎዱታል” ሲል አሳስቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *