Home / Social Affairs / የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያን ስምምነት “እየጣሰ ነው”፣ “የትግራይን ህዝብ እየገፋ ነው” ሲል ህወሓት ከሰሰ

የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያን ስምምነት “እየጣሰ ነው”፣ “የትግራይን ህዝብ እየገፋ ነው” ሲል ህወሓት ከሰሰ

የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያን ስምምነት እየጣሰ ነው፣ የትግራይን ህዝብ እየገፋው ነው ሲል ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለአምስት ቀናት ሲያካሂደው የነበረውን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ማጠናቀቁን ተከትሎ ሚያዚያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ማዕከላዊ ኮሚቴው “ይህ አካሄድ መሻሻል አለበት ብሎ ያምናል” ያለው መግለጫው “የፕሪቶርያው ስምምነት ተከብሮ ሁለቱ ፈራሚዎች በፖለቲካዊ ውይይት እና መግባባት በጋራ መስራት አለባቸው የሚል እምነት እንዳለውም” ገልጿል፣ “እንደሁልጊዜው ዝግጁ መሆኔም ይታወቅልኝ” ብሏል።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው የፌደራል መንግስት “በትግራይ ህዝብ በላዩ ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች እያወጣ ነው፣ ብቻውን በተናጠል የሚወስንባቸውን ሁኔታዎች በስፋት እየታየ ነው” ሲልም ተችቷል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መጋቢት 29 ቀን እስከ ሚያዚያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ያለፉት ስድስት ወራት ስራዎቼን ገምግሚያለሁ የቀጣይ ስድስት ወራት ስራ እቅዶቼን አስቀምጫለሁ ብሏል።

የትግራይ ህዝብ በጦርነቱ የደረሰበት ጉዳት እንዳይበቃ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላም ጉዳቱ በሌላ መልኩ እንዲቀጥል ተደርጓል ብሏል፤ ከውስጥ እና ከውጭ በመተባበር የትግራይን ህዝብ አንድነት ለመበተን እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር፣ ነገር ግን እንቅስቃሴዎቹ እና ሴራዎቹ መክሸፍ ጀምረዋል ሲል ገልጿል።

የትግራይን ህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ለመመለስ የጊዚያዊ አስተዳደሩ በሚያካሂዳቸው እንቅስቃሴዎች ታሪካዊ ግዴታየን እወጣለሁ ብሏል።

“የባከነውን ግዜ በማካካስ በወራሪዎች ስር የሚገኘውን ህዝባችንን ነጻ ለማውጣት፣ ግዛታዊ አንድነታችንን ለማስጠበቅ፣ የተሰደደ እና የተፈናቀለ ህዝባቸንን ወደ ቀየው ለማስመለስ፣ ክልሉ እንዲያገግም ለማድረግ እና መልሶ ለመገንባት፣ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር የበለጠ እድል እየተፈጠረ ነው ብሎ እንደሚያምን” ህወሓት በመግለጫው አስታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *