አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/2016 ዓ.ም፡- የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለመዘገብ አዲስ አበባ የተገኘው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ በኢትዮጵያ ሁከት ለመፍጠር በማሴር ወንጀል ተጠርጥሮ መታሰሩ ተገለጸ።
የአፍሪካን ኢንተለጀንስ ድረገጽ ዘጋቢው አንቶንዮ ጋሊንዶ ሲቪል በለበሱ የደህንነት ሰዎች ከሆቴሉ በቁጥጥር ስር ውሎ መወሰዱን አስታውቋል።
አለምአቀፉ የጋዜጠኞች ተቆርቋሪው ተቋም ሲፒጄ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኛውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቁት ዛሬ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ለእስር የተዳረገው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባለስልጣን የሆነውን ባቴ ኡርጌሳን ቃለመጠይቅ እያከናወነ ባለበት ግዜ መሆኑን ከጠበቃው ታምሩ ወንድም አገኘሁ ያገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ሲፒጄ አስታውቋል።
የጋዜጠኝነት ስራውን እየሰራ ባለበት ወቅት ያለአግባብ ከህግ ውጭ ለእስር የተዳረገው አንቶንዮ ጋሊንዶ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊለቀቅ ይገባል ሲሉ የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር አንጌላ ኩንታል መግለጻቸውን ጠቁሟል። የአንቶንዮ ጋሊንዶ መታሰር ኢትዮጵያ ለጋዜጠኞች ምን ያክል ምቹ አለመሆኗን ማሳያ ነው፣ የጋዜጠኝነት ስራቸውን በመስራታቸው ምክንያት ብቻ ስምንት የሚሆኑ ጋዜጠኞች በእስር ላይ ይገኛሉ፣ ያለምንም ቅድመሁኔታ ሊፈቱ ይገባቸዋል ሲሉ ሃላፊው መናገራቸውንም ሲፒጄ በመግለጫው አመላክቷል።
ሀሙስ የካቲት 14 ቀን 2016 በቁጥጥር ስር የዋለው የአፍሪካ ኢንተለጀንስ ጋዜጠኛው አንቶንዮ ጋሊንዶ ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም የቦሌ ምድብ ችሎት መቅረቡን እና የተመሰረተበትም ክስም የፌደራል መንግስቱን በትጥቅ ለመጣል ከሚታገሉ ሁለት ታጣቂ ቡድኖች (መንግስት ሸኔ ብሎ ከሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና ከፋኖ ሀይሎች) ጋር በማበር በመዲናዋ ሁከት ለመፍጠር በማሴር የሚል መሆኑን ጠቁሟል።
ጠንካራ ክስ ቢመሰረትበትም ፖሊስ ያቀረበው ምንም አይነት ማስረጃ የለም ሲሉ ጠበቃው እንደነገሩት ሲፒጄ በመግለጫው አካቷል።